የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሃገራችን አዲስ ውጥን ሲሆን በአፍሪካም በአይነቱ የመጀመሪያው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ራዕይ ዋላ ቀር እርሻ ላይ የተመሰረተውን የሃገሪቱ ግብርና ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ከገበሬው እስከ ነጋዴው፣ ከነጋዴው እስከ አቀናባሪው፣ ከአቀናባሪው እስከ ላኪው ሁሉንም ተገበያዮች የሚያገለግል አዲስ የግብይት ስርዓት መፍጠር ነው፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የገበያ አስተማማኝነትን፣ ደህንነትንና ቅልጥፍናን በማምጣት የወደፊቷን ኢትዮጵያ የሚያሳይ ገበያ ነው፡፡ ገበያው በምርቱ ዘርፍና በኢንዱስትሪው ማለትም በትራንስፖርት፣ በአቅርቦት፣ በባንክና በፋይናንስ አገልግሎት ዘርፎችና ሌሎች መካከል ተመጣጣኝ የሆነ እድገት የሚኖርበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሁሉም ምርት ተገበያዮች ምርት በማከማቸት፣ የጥራት ደረጃ በማውጣት፣ በማሻሻጥ፣ ከስጋት ነጻ የሆነ ክፍያና ርክክብ በመፈጸም የሚፈልጉትን አስተማማኝ የሆነ ጥበቃ ያደርጋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለሁሉም ተገበያዮች ወቅታዊ የገበያ መረጃ በመስጠት ተዓማኝነትና ግልጽነትን ይፈጥራል:: ይህንም የሚያደርገው ለግብይት፣ ምርት ለማከማቸት፣ ለክፍያና ርክክብ እንዲሁም ለቢዝነስ ግንኙነትና ለውስጣዊ ግንኙነቶች በግልጽ የሚታዩ ህጎችን በማስቀመጥ ነው፡፡ የምርት ገበያው የገበያ አስተማማኝነትን የሚፈጥረው በ3 ዋና ዋና ደረጃዎች ሲሆን እነሱም በምርቱ፣ በክፍያ እና በተገበያዮች ነው፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ግብይት የጀመረው ሚያዚያ 2001 ዓ.ም. ሲሆን ስራውን ሲጀምርም ለግብረናውና ለንግዱ ኢንዱስትሪም የአባልነት ግብዣ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በዘመናዊ ግብይቱ ተጠቃሚ የሚደርገው ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ስትገበያይባቸው በቆየችባቸው ምርቶች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ባህላዊ ከሆነው የግብይት ስርዓት ወደ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት ለመለወጥ ትፈልጋለች፡፡ ይህ ደግሞ በግብይትና ምርት ሂደቶች ላይ ያተኩራል፡፡
ምርት ገበያው ከመቋቋሙ በፊት በኢትዮጵያ የነበረው የእርሻ ውጤቶች ግብይት ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቅና ስጋት የተሞላበት ነበር፡፡ መጭበርበርን በመፍራት ከጠቅላላው ምርት አንድ ሦስተኛው ብቻ ለግብይት በሚቀርብበት ሀገር ሻጮችና ገዥዎች የሚገበያዩት የሚያውቁትን እያፈላለጉ ነው የሚገበያዩት፡፡ ግብይት የሚካሄደው ምርቱን በዓይን በመመልከት ብቻ ነበር፡፡ ለምርት ጥራትና ብዛት መተማመኛም አልነበረም፡፡ ይህ ደግሞ የገበያ ዋጋን በማናር በተጠቃሚው ላይ የዋጋ ጫና አሳድሯል፡፡ የሃገራችንን ምርት 95 በመቶ የሚያመርቱት አነስተኛ ገበሬዎች ታዲያ በቂ የገበያ መረጃ ስለማይኖራቸው በሚያውቁት የገበያ ቦታ ነጋዴው በቆረጠላቸው ዋጋ ይሸጡ ነበር:: ተደራድሮ በተሸለ ዋጋ መሸጥና የገበያውን ስጋት መቀነስ አይችሉም ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዲስ አሰራር በመዘርጋት ሁሉም ተገበያይ አስተማማኝ የሆነ ግብይት እንዲያካሂድ አስችሏል፡፡ ይህ የገበያ ስርዓት ገዥና ሻጭ በፍጥነት እንዲገናኙና እንዲገበያዩ ያደርጋል፡፡ የሁለቱንም ፍላጎት በመጠበቅ የኢትዮጵያን እርሻ ወደ አዲሱ ሚሊኒየም ማሸጋገሪያውና ግልጽነት፣ ውጤታማነትና በአዳዲስ ፈጠራዎች የተላበሰ ገበያ መፍጠሪያው ጊዜ አሁን ነው፡፡ በዓለም ዓቀፉ ገበያም ቦታ እንዲኖራት ማድረጊያ ጊዜውም አሁን ነው፡፡